አጀማመር

የዋገበታ የወንጌል አገልግሎት ከቀጬራ ቃ/ሕ አጥቢያ ቤ/ክ መካሄዱ ታሪካዊ መሠረት ያለው ነው። ይሀውም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትመሠረት ምክንያት የነበሩትና እንደመጋቢም እንደአስተማሪም ሆነው ያሳደጓት ወንጌላዊ ጉራቻ ህምበጎ መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ. ም. ወደጌታ ተሰበሰቡ። በሽኝታቸውም ቀን የቀጬራ ቤተ ክርስቲያን በአባባ ጉራቻ የተጀመረውን የወንጌል አገልግሎት ለማስቀጠል እገዛ እንደምትፈልግ በግልጽ አስታውቃ ነበር። ለዚህም የወንጌላዊ ጉራቻ ልጆችና ከቤተ ክርስቲያኒቱ አብራክ የወጡ ልጆች አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ። ከቤተክርስቲያኒቱ አብራክ የወጡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ልጆችዋም ቀደም ሲልም ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቱን ሲደግፉ የኖሩ ቢሆንም አሁን ደግሞ ከአባባ ጉራቻ ቤተሰብ ጋር በመሆን “ዋገበታ የወንጌል አገልግሎት” በሚል ሥያሜ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መደበኛ አገልግሎት ጋር አቀናጅቶ እንዲከናወን ይህ የአገልግሎት መርሀ-ግብር ተነደፈ።

ታሪካዊ አጀማመሩ

በ1920ዎቹ ውስጥ ወንጌል ወደ አካባቢው ሲደርስ ቀድመው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ከሰይጣን መንግሥት ለማምለጥ የታደሉ በጣት የሚቆጠሩ አባቶችና እናቶች ነበሩ። ከነርሱም መካከል የዋገበታው ወንጌላዊ ጉራቻ ህምበጎ እና የዳነቶራዋ ወይዘሮ ሣራ ግንዶሴ ይገኙ ነበር። ወይዘሮ ሣራ ከወንጌላዊ ጉራቻ ጎን በመሰለፍ ወንገልን ለማድረስ ለ16 ዓመታት ብርቱ ተጋድሎ ካደረጉ በኋላ በ1962 ዓ. ም. ወደጌታ ተሰብስበዋል። ወንጌላዊ ጉራቻ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1935 ዓ. ም. በ17 ዓመት ዕድሜአቸው ክርስቶስ ኢየሱስን ለመቀበል የታደሉ ሲሆን ከ1937 ዓ. ም. ጀምሮ ዘመናቸውን ሁሉ ወንጌልን ካገለገሉ በኋላ በመስከረም 24 2013 ዓ. ም. ወደጌታ ዕቅፍ ተሰበሰቡ።

ወንጌላዊ ጉራቻ አብዛኛውን የዕድሜአቸውን ዘመን ከትውልድ አካባቢያቸው ርቀው ሲያገለግሉ ቆይተው ዕድሜአቸው ገፍቶ ጉልበታቸው ሲቀንስ ወደ አገርቤት ተመለሱ። ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያደርጉ እንደነበረው ግን እሁድ እሁድ ከዋገበታው ቀጬራ ተነሥቶ ተራራውን በመውጣት ወደ ቀንቆ ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ ለማምለክ ግን አቅማቸው አልፈቀደም ነበር። በመሆኑም ይህቹ እናት ቤተክርስቲያናቸው በነበራት የቤተ ክርስቲያን ተከላ ራዕይ መሠረት የወንጌላዊ ጉራቻ የትውልድ መንደር በሆነችው በቀጬራ መንደር ቤተ ክርስቲያን እንዲትተከል ወሰነች። እሳቸውም ከመሬት ይዞታቸው ከፍለው በመስጠት በ1989 ዓ. ም. የቀጬራ አጥቢያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን በሶስት ጥንድ ቤተሰቦችና በአራት ወጣቶች አባልነት ተቆረቆረች። ወንጌላዊ ጉራቻም እንደመጋቢም እንደአስተማሪም በማገልገል በእግዚአብሔር ጸጋ ቤተ ክርስቲያኒቱን በማሳደግ ድርሻቸውን አበረከቱ። ባሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወጣቶችን ጨምሮ 400 የሚሆኑ ምዕመናን አሏት።

ወንጌላዊ ጉራቻ ዕድሜአቸው እየተገባደደ ሲሄድ በዋገበታ የተጀመረው የወንጌል አገልግሎት ቀጣይነት ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባቸው ነበር። ይህንንም በየጊዜው ለልጆቻቸው ይገልጹ ነበር። በተለይም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ወይም የልጆች ትምህርት ቤት ቢቋቋም የሚል ትልቅ መሻት ነበራቸው። ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሰጡት የጸሎት ቤት መሥሪያ ቦታ በተጨማሪ ለነዚሁ አገልግሎቶች እንኳ ተጨማሪ ቦታ ከመስጠት ወደኋላ እንደማይሉ ይታመን ነበር። ለምሳሌ ያህል ይህንኑ ራዕያቸውን በደቡብ አፍሪካ ለምትኖረው ልጃቸው ለፓስተር አረጋሽ ጉራቻ አካፍለዋት፣ እርስዋም መደበኛ የጸሎት ፕሮግራም ይዛ ለዓመታት እየጸለየች ራዕዩን ለሌሎች ወገኖችም ከማካፈሏም ባሻገር ከነዚያ ወገኖች መካካልም አንዳንዶቹ ዋገበታ ድረስ ደርሰው ወንጌላዊ ጉራቻን ለማግኘትና ቤተ ክርስቲያኒቱንም ለመጎብኘት ዕድል አግኝተው ነበር።

በመስከረም 29 2013 ዓ. ም. የወንጌላዊ ጉራቻ የቀብር ሥነ ሥርዓት በተከናወነበት ዕለት ለሽኝታቸው የመጣ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ሥፍራ የቀጬራዋ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አንድ ድንገተኛና ልብ የሚነካ ጥያቄ ለወንጌላዊ ጉራቻ ልጆች አቀረበች። ይሀውም “ከመካከላችሁ እርሳቸውን የሚተካ አንድ ሰው ስጡን” የሚል ነበር። ጥያቄው ሰው ከመወከል ያለፈና አገልግሎትን የማስቀጠል ጉዳይ መሆኑን የተገነዘቡት ልጆቻቸውም በሰዓቱ ወንድማቸውን እሼቱ ጉራቻን ወክለው የሰጡ ቢሆንም ታላቅ የወንጌል ሸክም እንደተጣለባቸው በመገንዘብ ይህንኑ ኃላፊነት ለመወጣት ጌታ ምሪት እንዲሰጣቸው መደበኛ የጸሎት ፕሮግራም በመያዝ መጸለይ ጀመሩ።

ከአንድ ዓመት የጸሎት ቆይታ በኋላ በመስከረም ወር 2014 ዓ. ም. ለጸሎታቸው መልስ የሆነ ሁኔታ በዋገበታ ተፈጠረ። ይሀውም፣ በሃዘን ላይ የቆዩትን እናታቸውን እማማ ዘነበችን ለመጎብኘት ልጃቸው ፓስተር አረጋሽ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ዋገበታ ትመጣለች፣ እዚያም በቆየችባቸው ሶስት ሳምንታት ውስጥ፣ እርሷኑ ለመጠየቅ ከሚመጣው ዘመድ አዝማድና ከክርስቲያን ወገኖች ጋር አብራ የእግዚአብሔርን ቃል በማካፈል መጸለይ ጀመረች። በነዚሁ ቀናት ውስጥ ከቃሉ ጀርባ የእግዚአብሔር መንፈስ በሥፍራው በመገኘቱ ለሀዘንተኞች፣ መጽናናት፣ ለብዙዎች ደግሞ መንፈሳዊ መነቃቃት ሲሆን፣ አንዳንዶችም ከሰይጣን እሥራት ነጻ ወጡ። በዚሁ የቤተሰብ ጸሎት ላይ ጥቂት የቀጬራ ቃለ ሕይወት አጥቢያ ቤ/ክ አባላትና መሪዎችም ተካፍለው ነበር።

ይህንኑ የቤተሰብ ጸሎት ተከትሎም በአካባቢው የቃለ እግዚአብሔርና የጸሎት ጥማት እንደተፈጠረ ፓስተር አረጋሽና የቀጬራ አጥቢያ ቤ/ክ መሪዎች አስተዋሉ። በመሆኑም ሰፋ ያለ የጸሎት ፕሮግራሙ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ ደረሱ፣ ቀደም ሲል ተጋብዞ ያገለገለውንም አገልጋይ እንደገና በመጋበዝ በቤተ ክርስቲያን የቃሉና የጸሎት ሥልጠና በቤተ ክርስቲያን ተካሄደ፣ በዚህኛውም ፕሮግራም ላይ የጌታ የእግዚአብሔር መገኘት ስለነበረ አሁንም ብዙ መንፈሳዊ መነቃቃት ሆነ፣ ብዙዎችም ከአጋንንት እስራት ተፈቱ (ምስክርነቱን በቀጣይነት ቤተክርስቲያኒቱ እንደምታዘጋጅ ይጠበቃል)። የወንጌላዊ ጉራቻ ቤተሰብና የቀጬራ ቃ/ሕ ቤተክርስቲያን በነዚያ ሳምንታት ውስጥ የታየውን የጌታ ሥራ እንደጸሎታቸው መልስ በመቁጠር፣ የቃለ እግዚአብሔርና የጸሎት ሥልጠና እንደዋነኛ የአገልግሎቱ አካል ሆኖ እንዲቀጥል በአንድ ሃሳብ ተስማሙ። በዚህም መሠረት የቀጬራ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የወንጌላዊ ጉራቻን ቤተሰብ ጨምሮ ከአብራካቸው ከወጡትና በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ካሉት ልጆቻቸው ጋር በመሆን አገልግሎቱን ለማስቀጠል ቆርጠው ተነሥተዋል።

የአገልግሎቱን የፕሮግራሞች ዕቅድ ለማየት እዚህ ይጫኑ።