ፕሮግራሞቻችን

የዋገበታ የወንጌል አገልግሎት ፕሮግራሞች በሁለት ሌመደቡ የሚችሉ ናቸው፣ እነርሱም፣ ቃለ-እግዚአብሔርና ጸሎት እና ሁለንተናዊ አገልግሎት ናቸው። ሁለንተናዊ አገልግሎት የተባሉት ሥራዎች እንደመስበክና እንደመጸለይ ወንጌል በቀጥታ የሚሰበክባቸው ባይሆኑም በተዘዋዋሪ በኅብረተሰቡ ላይ ትርጉም ያለው ተጽዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው። እያንዳንዱን ጠጋ ብለን ብናያቸው፦

 1. ቃለእግዚአብሔር ጸሎት አማኞች በእግዚአብሔር ቃል ሥር እንዲሰድዱና ትርጉም ያለ ጸሎት መጸለይን እንዲለማመዱ ያግዛል። እነዚህ ሁለቱ የማይነጣጠሉ አገልግሎቶች ስለሆኑ በተቀናጀ መልኩ ይደራጃሉ።
 2. ሁለንተናዊ አገልግሎት የእግዚአብሔርን ቃል በቀጥታ ከማስተማርና ከመጸለይ ጎን ለጎን የሰዎችን ሥነ-ልቦናዊ ሆነ ቁሳዊ ፍላጎት መዳሰስ እንዲቻል የሚከተሉት የሁለንተናዊ አገልግሎት ተግባሮችም ይከናወናሉ፦
  • ሀ) የልጆች የመሠረተ ትምህርት የሚቀጥለውም ትውልድ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሥር የሰደደና፣ ደግሞም እንደሚገባ የሚጸልይ ይሆን ዘንድ ሕጻናትና ልጆች ይህንኑ ከለጋነታቸው ጀምሮ እንዲለማመዱ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ያግዝ ዘንድ በቤተክርስቲያን ውስጥ ወንጌል ተኮር የሆነ የልጆች የመሠረተ ትምህርት ፕሮግራም ይካሄዳል።
  • ለ) የሚዲያ አገልግሎት ከሥልጠናውና ከመሠረተ ትምህርቱ በተጨማሪ፣ ሰዎች መንፈሳቸውንና አእምሮአቸውን እንዲያንጹ ለማገዝ የሚዲያ አገልግሎት ይካሄዳል። ለዚህም፣ የሚነበቡ [ጽሁፎችን]፣ የሚደመጡ [ኦዲዮዎችን]፣ ወይም የሚታዩ [ቪዲዮዎችን/ፊልሞችን] በጥንቃቄ መርጦ በማቅረብ በማዕከል በአካል ተገኝተውም ይሁን እንደቤተ መጻህፍት በተውሶ እየወሰዱ እንዲጠቀሙ የሚያስችል የሚዲያ ማዕከልም ይደራጃል።
  • ሐ) እምነት በተግባር መጽሐፍ ቅዱስ በሥራ የማይገለጥ እምነት የሞተ ነው ይላል። ከቃሉና ከጸሎት ሥልጠናው ጋር በተቀናጀ ሁኔታ እምነታችንን በተግባር ለመግለጽ በኑሮ የጎላ እጥረት ያለባቸውን የኅብረተሰብ አባላት የመጎብኘት ተግባር ይከናወል።
  • መ) ተዛማጅ ሥልጠናዎች የሰዎችን ኑሮ ለማሻሻል ይረዳሉ ተብለው በሚታመኑ በተመረጡ ጥቂት ጉዳዮች ላይ ሥልጠናዎች ይካሄዳሉ።

የአገልግሎቱ አካሄድ/አቀራረብ፦

የቃልና የጸሎት አገልግሎቱ ተጽዕኖው ቦግ ብሎ ወዲያው የሚጠፋ እንዳይሆንና፣ ሰዎች ቃሉንና ጸሎትን ለዘለቄታው በግላቸው መለማመድ ይችሉ ዘንድ በሥልጠና መልክ የሚከናወን ይሆናል። ሥልጠና ከተሰጠ በኋላም ሰዎች የሠለጠኑበትን ነገር ሲለማመዱ በየስድስት ወሩ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል። ሁለንተናዊ አገልግሎትን በተመለከተየልጆች መሠረተ ትምህርት ፕሮግራም ጥራቱ ከመንግስት ት/ቤቶች በላቀ እንጂ ባልተናነሰ ደረጃ የሚሰጥ ሆኖ የቃለ እግዚአብሔርና የጸሎት ልምምድም ለልጆች በሚመጥን መልኩ ከመሠረተ ትምህርት ጋር ተቀናጅቶ ይከናወናል። ይህም ከሰንበት ትምህርት በተጨማሪ ከሰኞ እስከ አርብ ባሉ ቀናት የሚሰጥ ይሆናል። የሚዲያ አገልግሎቱም የአካባቢውን ኅብረተሰብ የሥራ ሰዓት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ (ለምሳሌ ሰዎች ከእርሻ ወይም ከአጨዳ ሥራ ተመልሰው በሚያርፉበት በምሽቱ ጊዜ) እንዲቀርብ የታሰበ እንደመዝናኛም እንደትምህርትም የሚያገለግል ፕሮግራም ይሆናል። እምነትን በተግባር መግለጽ የሚለውን አምላካዊ መርህ በተግባር ለመግለጽ፣ ከአብዛኛው የአካባቢው ኅብረተሰብ ይልቅ የሆኑ ለኑሮ የሚያስፈልጉ በጣም መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ ለማግኘት የሚቸገሩ ቤተሰቦችን ለማበረታታት በየሥልጠናው ወቅት ለጥቂቶቹ ማቴሪያላዊ ድጋፍ ይደረጋል። ተዛማጅ ሥልጠናዎቹ ሲታቀዱ በተሳታፊዎች ህይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ የሚያመጡ መሆናቸው አስቀድሞ መረጋገጥ አለበት፣ ልክ እንደ ቃልና ጸሎቱ ሥልጠናው ሁሉ፣ የተዛማጅ ሥልጠና ሰልጣኞችም የሰለጠኑበትን ዕውቀት በግላቸው በተግባር ሲያውሉ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግበት መንገድ ይበጃል። የሰልጣኞቹ ጥረትና ውጤቱም በየስድስት ወሩ እየተገመገመ መሻሻያ የፕሮግራም ይደረግበታል።

የአገልግሎቱ ዕቅድ፦

የአገልግሎቱ የሚቀጥለው የሦስት ዓመት (መስከረም 2014 – ነሐሴ 2016 ዓ. ም) ዕቅድ በጥቅሉ እንደሚከተለው ይሆናል፦

 1. የቃለ እግዚአብሔርና የጸሎት ሥልጠና፦ በየስድስት ወሩ አንድ ጊዜ፣ በድምሩ 5 የቃለ እግዚአብሔርና የጸሎት ሥልጠናዎች ይካሄዳሉ።
 2. ሁለንተናዊ አገልግሎት፦
  • የልጆች መሠረተ ትምህርት፦ ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትገኝበት ኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ ከ1ኛ ክፍል በታች ላሉ ልጆች ክቃለ እግዚአብሔርና ከጸሎት ጋር የተቀናጀ መሠረተ ትምህርት ይሰጣል። በዚሁ ፕሮግራም ውስጥ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላገኙ ጥቂት ተማሪዎችም የማበረታቻ ሽልማት ይሰጣቸዋል።
  • የሚዲያ አገልግሎት፦ መንፈስንና አዕምሮን ለማነጽ የሚያስችሉ በጽሁፍ፣ በኦዲዮ፣ በቪድዮ ወይም በፊልም መልክ የተዘጋጁ ሚዲያዎች ለቤተክርስቲያኒቱ አባላትና እንደአግባቡም ለኅብረተሰብ አባላት ለማቅረብ የሚያስችል የሚዲያ ማዕከል ተደራጅቶ አገልግሎት ይሰጣል።
  • እምነት በተግባር፦ በየስድስት ወሩ ከሚካሄደው የቃልና የጸሎት ሥልጠና ወቅት ጥቂት የተቸገሩ ቤተሰቦች ተመርጠው የገንዘብም ሆነ የማቴሪያል ድጋፍ ይሰጣቸዋል።
  • ተዛማጅ ሥልጠናዎች፦ በየስድስት ወሩ ከሚካሄደው የቃልና የጸሎት ሥልጠና ጎን ለጎን በአንድ መሠረታዊ የኅብረተሰብ ችግር ላይ መፍትሔ የሚሆን ሥልጠና ይካሄዳል።

የሚጠበቅ ውጤት፦

በዚህ አገልግሎት አማካይነት የሚካሄዱት እንቅስቃሴዎችና ጥረቶች ሁሉ (የቃሉና የጸሎት ሥልጠናዎችም ሆኑ ሁለንተናዊ አገልግሎቶች) ጌታን የመጠባበቂያ ሂደቶች እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራለን። ጌታ ሁሌም ከቃሉ በስተጀርባ አለ፣ ስለሆነም በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ጠለቅ ብለን በገባንና ለጸሎትና ለአምልኮ ልባችንን በከፈትን መጠን የእግዚአብሔር መንፈስ በመካከላችን በኃይል እንደሚገለጥ እናምናለን። ይህም ከርስቶስን የማያውቁ ወገኖችም ክርስቶስን በግላቸው እንዲያውቁ ይጋብዛቸዋል ብለን እናምናለን። የሰዎች አዕምሮና አስተሳሰብ በተለወጠ መጠንም ኅብረተሰብ ውስጥ ሰላም ብልጽግና እንደሚሰፍንም እናምናለን።